"እብዱ" አውግቸው
ሕሩይ ሚናስ እውነተኛ ስሙ ነው - የሚታወቀው ግን ራሱ ለራሱ እና ለኣባቱ ጭምር ባወጣው ስም ነው። ሕሩይ አንድ ወቅት ላይ አበደ! ሁናቴውን ተናፋቂው ኮከብ ጋሽ ኃይለመለኮት እንዲህ ያወሳዋል።
★በዚያች የንባ
ብ ቤት ስመላለስ ከአቀማመጥ ጀምሮ በመልክ ጭምር የሚመሳሰሉት ጋሽ ስብሐት ለኣብ እና እርሱ ያላቸውን ፍቅር እና ከበሬታ ስለማውቅ፥ የእርሱን ማበድ ስሰማ ለጋሽ ስብሐት በጣም ደነገጥኩ። ጭራሽ ደግሞ ሕሩይ ሸሚዙን ቀዶ ሲሮጥ፣ ከራሱ ጋር ሲለፈልፍ አየሁት፥ ወደዚያች የጥበብ ቤታችን ሄድኩ፥ እንዳሰብኩትም ሚናስ ባይኖርም ጋሽ ስብሐት መጽሐፍ ይዞ ሚናስ ቤት ተቀምጧል። እንዴት እንደምጀምር ስፈራ ስቸር ቆይቼ ...
"ጋሽ ስብሐት፥ ሕሩይ እኮ አበደ!" አልኩት።
የሚያሳየውን የአካል ለውጥ ስጠብቅ ጋሽ ስብሐት ሳይሞቀውም፣ ሳይበርደውም ስመለከት ከእኔ ቀድሞ የነገረው ሰው ይኖራል ብዬ አሰብኩ፥ ወዲያው ግን ጋሽ ስብሐት ካቀረቀረበትም ቀና ሳይል፦
"ደግ፣ እሰይ" አለኝ ጭራሽ ምንም ሳይመስለው።
"ጋሽ ስብሐት ሰምተኸኛል? ሕሩይ አበደ፣ ጨርቁን ጣለ፣ ብቻውን መንገድ ለመንገድ እየጮኸ አየሁት ነው እኮ የምልህ" አልኩት።
"እንኳን፣ እሰይ" አለኝ በድጋሚ።
"ምነው? ለምን?" ብለው።
"በቃ ተገላገለ፥ ነፃ ወጣ!" አለኝ።★
ሲል ሲያወራ ቢውል በሚያስመኝ አንደበቱ ወቅቱን ይገልፀዋል።
ሕሩይ በበኩሉ በዚያ የ"እብደት" ጊዜው ውስጥ ሳለ ያየውን፣ ድንገት በሕሊናው ይከሰት የነበረውን፣ የእብደት ዓለም አስተሳሰብ "እብዱ" በሚል ርዕስ ከትቦ ለንባብ አበቃው።
ሕሩይ ሚናስ - ወይም ራሱ ለራሱ ባወጣው ስም ደግሞ ኣውግቸው ተረፈ!
ረዥም እድሜ ከምሉዕ ጤና ጋር!
※※※
የሰው ልጅ እስረኛ ነው።
† በሃይማኖት ብንሄድ ስጋ የነፍስ እስር ቤት ናት
† በስነልቡና ብንሄድ ሰው የሃሳቡ እና ምኞቱ እስረኛ ነው
† በማህበራዊ ብንሄድ ሰው የህግ እና ልማድ እስረኛ ነው
ነፃ የሚያወጡን ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው የሚል አመለካከት ነበረኝ። በዚህ ፅሁፍ ስብሐት ሶስተኛውን ከሰተልኝ። ሞት ግዜያዊ ነፃነት ሲያጎናፅፈን አብርሆት(enlightenment) ደግሞ ፍፁም ነፃነት ይሰጠናል። ሞት ከስጋ እስር ነፃ ሲያወጣን አብርሆት ከሃሳብ እና ምኞት እስር አውጥቶ የመንፈስ ነፃነት ይሰጠናል። የዘነጋሁት እብደትን ነበር። ይሄ በየመንገዱ ጨርቁን ጥሎ የሚንወላገደው እብድ ከብዙዎቻችን የተሻለ ነፃነት አለው። በእርግጥ ይህ ነፃነት ማህበራዊ ነው። ትልቁ አብነትም ግሪካዊ ዲዮጋን ነው። ይህ ጥንታዊ ፈላስፋ በብዙዎቻችን መስፈርት የለየለት ንክ ነበር። ዲዮጋን አንደኛውን ሰንሰለት ሰብሯል። He doesn't give a rat's ass what every Athenian thinks including Alexander the great. ጥሩ ወይስ መጥፎ የሚለው አንድምታ ሌላ ርእስ ሆኖ እብደት አንድ አይነት ነፃነት ነው።
ስብሐት ነገሮችን የሚያይበት አይኑ ዘወትር እንደደነቀኝ ነው። እሱ ራሱ ነፃ ነበር። ንክ አላልኩም!

Comments
Post a Comment